አዲስ ህይወት

አዲስ ህይወት

ልክ አዲስ አበባ እንደሚከፈት፣ በእምነትዎ የሚያድጉበት ሂደት አሁን ይጀምራል፡፡ አሁን የእግዚአብሔርን ፍቅር እና መመሪያ መለማመድ የሚጀምሩ ሲሆን ልክ ወደ በሰለ ክርስቲያን ሲያድጉ የተሻለ እና የበለጠ ይሆናል፡፡

ወደ እግዚአብሔር በመጠጋት መቆየትዎን ያረጋግጡ

ይህ እንዴት ይደረጋል? ደህና፣ እነዚህ ነገሮች በእርግጠኝነት ይረዱዎታል፡፡

  • በየቀኑ ይፀልዩ፣ እያንዳዱን ነገር ትንሽም ሆኑ ትልቅ ነገሮችን በፀሎት ጊዜ ለእግዚአብሔር ያጋሩ [1]፡፡
  • መፅሀፍ ቅዱስዎን በየቀኑ ያንብቡ፣ ብዙ ጊዜ ባይኖርዎትም እንኳን የመፅሀፍ ቅዱስ አንድ ክፍል ብቻም ቢሆን (ነገርግን ብዙ ባነበቡ ቁጥር ብዙ በረከት ከእርሱ ያገኛሉ[2]፡፡
  • የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነ በመፅሀፍ ቅዱስ ውስጥ ምን እንዳለ ትኩረት ያድርጉ፡ የሰዎች ትምህርት እና ሀሳቦች ከእግዚአብሔር ቃል ያነሱ ናቸው፡፡[3]፡፡
  • ኑሮዎን በጥሩ እና ታማኝ በሆነ መንገድ ለመኖር ይሞክሩ፡፡ ይህም ለእግዚአብየሔር ደስታ ነው፡፡ መጥፎ ልምዶችን እና ኃጢአቶችን ይስበሩ፣ አግዚአብሔር ስለሚያይ በእያንዳንዱ ቀን ለእርሱ ለመኖር ይጣሩ [4]፡፡ እዚህ ጋር ለእርዳታ እና ለጥበብ ይፀልዩ፡፡
  • ጌታ ኢየሱስን ሁልጊዜ ለኃጢአቶች ይቅርታን ይጠይቁ (በምድር ላይ እስካሉ ድረስ ምንም እንኳን ጠንክረው ለመስራት ቢሞክሩም ትክክል አይሆኑም፣ ስህተቶች ይሠራሉ)[5]፡፡
  • ሌሎች አምልኮቶችን ወይም ጣኦቶችን የሚያመልኩ የነበረ ከሆነ ይህንን ስራ ያቁመ እና የጣኦት ሀውልቶችን ያጥፉ [6]፡፡
  • ቤተክርስቲያን ወይም የክርስቲያኖች ቡድንን ይቀላቀሉ፡ የትምህርት ክትትል በእምነትዎ እንዲበረቱ ይረዳዎታል፡፡ ( ልክ በእሳት ውስጥ ያለ እንጨት እየቀዘቀዘ እንዳይሄድ ወደ እሳቱ መጠጋት እንዳለበት ሁሉ[7]፡፡
  • ጌታ ኢየሱስ እንዲጠመቁ ይጠይቅዎታል፡፡ ይህም ምርጫዎን ህዝባዊ እውነታ እንዲኖረው ያደርጋል፡ ጥምቀት እንዲሰጥዎት ፓስተር፣ ቤተክርስቲያን ወይም ሌላ ክርስቲያን ይፈልጉ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጁ እንደሆነ ማመንዎን ምስክርነት ሲሰጡ እና እንደግል አዳኝዎ እና ጌታዎ መሆኑን ሲያውቁ፣ “በአብ በወልድ እና በመንፈስቅዱስ ስም፣ በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም” መጠመቅ ይችላሉ [8]፡፡
  • እምነትዎን ለሌሎች ሠዎች ያካፍሉ፡ የምስራቹ ለእያንዳንዱ ነው፣ ለራስዎ አያስቀምጡት[9]፡፡
  • ህይወትዎ እስከሚያበቃበት ድረስ አማኝ ሆነው ይቆዩ [10] ወይም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እስኪመጣ ድረስ [11]!

በህይወትዎ እግዚአብሔር እርስዎን እና ቤተሰብዎን ይባርክ፡ ወደ እርሱ መቅረብዎን ሲቀጥሉ፣ በህይወትዎ ይመራዎታል፣ እንዲሁም ጠንካራ እምነት ይስጥዎት፡፡ በእርሱ ላይ ሙሉ እምነት እንዲኖርዎት ያስችልዎት፡፡ በልብዎ ፍቅሩን፣ ደስታውን እና ውስጣዊ ሰላሙን ይስጥዎት፡፡  በምንም አይነት አጋጣሚዎች በህይወትዎ ውስጥ፡ እርሱ ከእርስዎ ጋር ነው!

ጠቃሚ ማስፈንጠርያዎች እንዲረዳዎት

ጠለቅ ያለ መረጃ የእግዚአብሔር ቃልን እንደ ምንጭ በመጠቀም ያንብቡ

ማጠቃለያውን ያንብቡ (ዋናው መግቢያ)

[1]

ደቀ መዛሙርቱ ሳይታክቱ ሁል ጊዜ መጸለይ እንደሚገባቸው ለማሳየት ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ ሉቃስ 18:1 NASV

ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በማናቸውም ሁኔታ አመስግኑ፤ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ለእናንተ ይህ ነውና። 1 ተሰሎንቄ 5:17-18 NASV

አንተ ግን ስትጸልይ ወደ ክፍልህ ግባ፤ በሩንም ዘግተህ በስውር ወዳለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የተደረገውን የሚያይ አባትህም ዋጋህን ይከፍልሃል። ስትጸልዩ፣ ከንቱ ቃላት በመደጋገም ጸሎታቸው የሚሰማላቸው እንደሚመስላቸው አሕዛብ ነገራችሁን አታስረዝሙ። እነርሱን አትምሰሏቸው፤ አባታችሁ ከመለመናችሁ በፊት ምን እንደሚያስፈልጋችሁ ያውቃልና። “እናንተ ግን እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ፤ “ ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን። የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን። እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል፣ በደላችንን ይቅር በለን። ወደ ፈተናም አታግባን ከክፉው አድነን እንጂ፣ መንግሥት፣ ኃይል፣ ክብርም፣ ለዘለዓለሙ ያንተ ነውና፤ አሜን።’ እናንተ የበደሏችሁን ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ ደግሞ እናንተን ይቅር ይላችኋል። ነገር ግን የሰዎችን ኀጢአት ይቅር የማትሉ ከሆነ፣ አባታችሁም ኀጢአታችሁን ይቅር አይልላችሁም። ማቴዎስ 6:6-15 NASV

በእግዚአብሔር ፊት ለመቅረብ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ ማንኛውንም ነገር እንደ ፈቃዱ ብንለምን እርሱ ይሰማናል፤ 1 ዮሐንስ 5:14 NASV

“ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ለምኑ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ ታገኛላችሁ፤ በር አንኳኩ ይከፈትላችኋል፤ ምክንያቱም የሚለምን ሁሉ ይቀበላል፤ የሚፈልግም ያገኛል፤ በር ለሚያንኳኳም ይከፈትለታል። ሉቃስ 11:9-10 NASV

እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳላችሁ፣ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታን መስጠት ካወቃችሁበት፣ የሰማዩ አባታችሁ ታዲያ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጥ!” ሉቃስ 11:13 NASV

በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ፣ ከምስጋናም ጋር ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ እንጂ ስለማንኛውም ነገር አትጨነቁ። ከማስተዋል በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም፣ ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል። ፊልጵስዩስ 4:6-7 NASV

በተስፋ ደስተኞች ሁኑ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ። ሮሜ 12:12 NASV

እግዚአብሔር ለሚጠሩት ሁሉ፣ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው። ለሚፈሩት ፍላጎታቸውን ይፈጽማል፤ ጩኸታቸውን ይሰማል፤ ያድናቸዋልም። መዝሙር 145:18-19 NASV

እናንተም ትጠሩኛላችሁ፤ ቀርባችሁ ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፤ እኔም እሰማችኋለሁ። እናንተ ትፈልጉኛላችሁ፣ በፍጹም ልባችሁም ከፈለጋችሁኝ ታገኙኛላችሁ፤ ኤርምያስ 29:12-13 NASV

‘ወደ እኔ ጩኽ፤ እኔም እመልስልሃለሁ፤ አንተም የማታውቀውን ታላቅና የማይመረመር ነገር እገልጥልሃለሁ፤’ ኤርምያስ 33:3 NASV

ስለዚህ ኀጢአታችሁን እርስ በርሳችሁ ተናዘዙ፤ ትፈወሱም ዘንድ አንዱ ለሌላው ይጸልይ። የጻድቅ ሰው ጸሎት ኀይል አለው፤ ታላቅ ነገርም ያደርጋል። ያዕቆብ 5:16 NASV

እንዲሁም ደግሞ መንፈስ በድካማችን ያግዘናል፤ እንዴት መጸለይ እንደሚገባን አናውቅም፤ መንፈስ ግን በቃላት ሊገለጥ በማይችል መቃተት ለእኛ ይማልድልናል። ሮሜ 8:26 NASV

[2]

ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው። መዝሙር 119:105 NASV

በድነታችሁ እንድታድጉ፣ አዲስ እንደ ተወለዱ ሕፃናት ንጹሑን መንፈሳዊ ወተት ተመኙ፤ 1 ጴጥሮስ 2:2 NASV

ጒልማሳ መንገዱን እንዴት ያነጻል? በቃልህ መሠረት በመኖር ነው። መዝሙር 119:9 NASV

እርሱ ግን፣ “ብፁዓንስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚታዘዙት ናቸው” አለ። ሉቃስ 11:28 NASV

ማንኛውንም ነገር ሳታጒረመርሙና ሳትከራከሩ አድርጉ፤ ይኸውም በጠማማና በክፉ ትውልድ መካከል ንጹሓንና ያለ ነቀፋ፣ ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች ሆናችሁ፣ እንደ ከዋክብት በዓለም ሁሉ ታበሩ ዘንድ ነው። የሕይወትንም ቃል ስታቀርቡ፣ በከንቱ እንዳልሮጥሁ ወይም በከንቱ እንዳልደከምሁ በክርስቶስ ቀን የምመካበት ይሆንልኛል። ፊልጵስዩስ 2:14-16 NASV

[3]

ቃልህ እውነት ነው፤ በእውነትህ ቀድሳቸው። ዮሐንስ 17:17 NASV

እንግዲያስ ትንቢታዊው ቃል ይበልጥ ተረጋግጦልናል፤ ሌሊቱ እስኪነጋና የንጋት ኮከብ በልባችሁ እስኪበራ ድረስ፣ በጨለማ ስፍራ ለሚበራ መብራት ጥንቃቄ እንደሚደረግ እናንተም ለዚህ ቃል ብትጠነቀቁ መልካም ታደርጋላችሁ። ከሁሉ አስቀድሞ ይህን ልታውቁ ይገባችኋል፤ በመጽሐፍ ያለው የትንቢት ቃል ሁሉ ማንም ሰው በገዛ ራሱ መንገድ የሚተረጒመው አይደለም፤ ምክንያቱም ትንቢት ከእግዚአብሔር የተላኩ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ተናገሩት እንጂ ከቶ በሰው ፈቃድ የመጣ አይደለም። 2 ጴጥሮስ 1:19-21 NASV

ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር ይጠቅማሉ፤ ይኸውም የእግዚአብሔር ሰው ለመልካም ሥራ ሁሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው። 2 ጢሞቴዎስ 3:16-17 NASV

ሣሩ ይደርቃል፤ አበባውም ይረግፋል፤ የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።” ኢሳይያስ 40:8 NASV

[4]

እንግዲህ፣ ወዳጆች ሆይ፤ ይህ የተስፋ ቃል ስላለን፣ ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ፤ እግዚአብሔርንም በመፍራት ቅድስናችንን ፍጹም እናድርገው። 2 ቆሮንቶስ 7:1 NASV

ስለዚህ ርኵሰትንና ተንሰራፍቶ የሚገኘውን ክፋትን አስወግዳችሁ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን፣ በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በትሕትና ተቀበሉ። ቃሉ የሚናገረውን አድርጉ እንጂ ሰሚዎች ብቻ ሆናችሁ ራሳችሁን አታታልሉ። ያዕቆብ 1:21-22 NASV

ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር የሚቻላችሁን ሁሉ አድርጉ፤ ለመቀደስም ፈልጉ፤ ያለ ቅድስና ማንም ጌታን ማየት አይችልም፤ ዕብራውያን 12:14 NASV

ነገር ግን የጠራችሁ እርሱ ቅዱስ እንደሆነ እናንተም በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፤ ምክንያቱም “እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ተብሎ ተጽፎአል። 1 ጴጥሮስ 1:15-16 NASV

እንግዲህ እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን ምሰሉ፤ ክርስቶስ እንደ ወደደን ራሱንም ስለ እኛ መልካም መዐዛ ያለው መባና መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር እንደ ሰጠ እናንተም በፍቅር ተመላለሱ። ማንኛውም የዝሙት ወይም የርኵሰት ወይም የስስት ነገር ከቶ በመካከላችሁ አይነሣ፤ ይህ ቅዱስ ለሆነው ለእግዚአብሔር ሕዝብ አይገባምና። የሚያሳፍርና ተራ የሆነ ንግግር፣ ዋዛ ፈዛዛም ለእናንተ ስለማይገባ በመካከላችሁ አይኑር፤ ይልቁንስ የምታመሰ ግኑ ሁኑ። ደግሞም ይህን ዕወቁ፤ ማንም አመንዝራ ወይም ርኩስ ወይም ስግብግብ ይኸውም ጣዖት አምላኪ በክርስቶስና በእግዚአብሔር መንግሥት ርስት የለውም። ማንም በከንቱ ንግግር አያታላችሁ፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቊጣ በማይታዘዙ ልጆች ላይ የሚመጣው በእንደዚህ ዐይነት ነገር ነው። ስለዚህ እንዲህ ካሉ ጋር አትተባበሩ። ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁ፤ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ። እንደ ብርሃን ልጆች ኑሩ፤ የብርሃኑ ፍሬ በበጎነት፣ በጽድቅና በእውነት ሁሉ ዘንድ ነውና። እንዲሁም ጌታን ደስ የሚያሰኘውን ፈልጉ። ኤፌሶን 5:1-10 NASV

እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ሰውነታችሁን ቅዱስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕያው መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፤ ይህም እንደ ባለ አእምሮ የምታቀርቡት አምልኮአችሁ ነው። መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሮአችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። ሮሜ 12:1-2 NASV

ስለዚህ ምድራዊ ምኞቶቻችሁን ግደሉ፤ እነዚህም፦ ዝሙት፣ ርኵሰት፣ ፍትወት፣ ክፉ ምኞትና አምልኮተ ጣዖት የሆነው መጐምጀት ናቸው። በእነዚህም ምክንያት የእግዚአብሔር ቊጣ በማይታዘዙት ላይ ይመጣል፤ እናንተም ቀድሞ በኖራችሁበት ሕይወት በእነዚህ ትመላለሱ ነበር፤ አሁን ግን ቊጣን፣ ንዴትን፣ ስድብን፣ ሐሜትንና አሳፋሪ ንግግርን የመሳሰሉትንም ሁሉ አስወግዱ፤ አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር አውልቃችሁ ስለ ጣላችሁ እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ። የፈጣሪውን መልክ እንዲመስል በዕውቀት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችኋል፤ በዚያ ግሪክ ወይም ይሁዲ፣ የተገረዘ ወይም ያልተገረዘ፣ አረማዊ ወይም እስኩቴስ፣ ባሪያ ወይም ጌታ ብሎ ልዩነት የለም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉም ነው፤ በሁሉም ነው። እንግዲህ የተቀደሳችሁና የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ምርጦች እንደመሆናችሁ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ ጨዋነትንና ትዕግሥትን ልበሱ፤ እርስ በርሳችሁ ተቻቻሉ፤ ከእናንተ አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ፤ ጌታ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም ሌላውን ይቅር በሉ። በእነዚህ ሁሉ ላይ ሁሉን በፍጹም አንድነት የሚያስተሳስረውን ፍቅርን ልበሱት። እንደ አንድ አካል ሆናችሁ የተጠራችሁበት የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይንገሥ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ። የክርስቶስ ቃል በሙላት ይኑርባችሁ፤ እርስ በርሳችሁ በጥበብ ሁሉ ተማማሩ፤ ተመካከሩ፤ በመዝሙርና በማሕሌት፣ በመንፈሳዊም ቅኔ በማመስገን በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ። በእርሱ በኩል ለእግዚአብሔር አብ ምስጋና እያቀረባችሁ፣ በቃልም ሆነ በተግባር የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት። ቈላስይስ 3:5-17 NASV

“ለመላው የእስራኤል ሕዝብ ጉባኤ እንዲህ ብለህ ተናገራቸው፤ ‘እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ። ዘሌዋውያን 19:2 NASV

“ ‘ራሳችሁን ቀድሱ፤ ቅዱሳንም ሁኑ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝና። ዘሌዋውያን 20:7 NASV

በዚህም ምክንያት በሙሉ ትጋት በእምነታችሁ ላይ በጎነትን ለመጨመር ጣሩ፤ በበጎነት ላይ ዕውቀትን፣ በዕውቀት ላይ ራስን መግዛት፣ ራስን በመግዛት ላይ መጽናትን፣ በመጽናት ላይ እውነተኛ መንፈሳዊነትን፤ በእውነተኛ መንፈሳዊነት ላይ ወንድማዊ መተሳሰብን፣ በወንድማዊ መተሳሰብ ላይ ፍቅርን ጨምሩ። እነዚህ ባሕርያት ተትረፍርፈው ቢኖሯችሁ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ ዳተኞችና ፍሬ ቢሶች ከመሆን ይጠብቋችኋል። እነዚህ ባሕርያት የሌሉት ግን የሩቁን የማያይ ወይም ዕውር ነው፤ ከቀድሞው ኀጢአቱ መንጻቱንም ረስቶአል። 2 ጴጥሮስ 1:5-9 NASV

[5]

ኀጢአታችንን ብንናዘዝ ኀጢአታችንን ይቅር ሊለን፣ ከዐመፃ ሁሉ ሊያነጻን እርሱ ታማኝና ጻድቅ ነው።
1 ዮሐንስ 1:9 NASV

እንግዲህ ምን እንላለን? ጸጋ እንዲበዛ ኀጢአት እየሠራን እንኑር? ከቶ አይሆንም፤ ለኀጢአት ሞተናል፤ ታዲያ እንዴት አድርገን ከእንግዲህ በእርሱ እንኖራለን? ሮሜ 6:1-2 NASV

ልጆቼ ሆይ፤ ይህን የምጽፍላችሁ ኀጢአት እንዳትሠሩ ነው፤ ነገር ግን ማንም ኀጢአት ቢሠራ፣ በአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኀጢአታችን ማስተስረያ ነው፤ ይኸውም ለዓለም ሁሉ ኀጢአት እንጂ ለእኛ ብቻ አይደለም። 1 ዮሐንስ 2:1-2 NASV

ኀጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝና የሚተወው ግን ምሕረትን ያገኛል። ምሳሌ 28:13 NASV

ኀጢአቴን ለአንተ አስታወቅሁ፤ በደሌንም አልሸሸግሁም፤ ደግሞም “መተላለፌን ለእግዚአብሔር እናዘዛለሁ” አልሁ፤ አንተም የኀጢአቴን በደል፣ ይቅር አልህ። ሴላ መዝሙር 32:5 NASV

በእርሱም እንደ እግዚአብሔር ጸጋ ባለጠግነት መጠን፣ በደሙ በተደረገ ቤዛነት፣ የኀጢአትን ይቅርታ አገኘን፤ ኤፌሶን 1:7 NASV

ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ፣ እኛም በብርሃን ብንመላለስ እርስ በእርሳችን ኅብረት አለን፤ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኀጢአት ሁሉ ያነጻናል። 1 ዮሐንስ 1:7 NASV

[6]

እንግዲህ በላይ በሰማይ፣ በታችም በምድር እግዚአብሔር እርሱ አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) መሆኑን ዛሬ ዕወቅ፤ በልብህም ያዘው፤ ሌላም የለም። ዘዳግም 4:39 NASV

“የሰው እጅ የቀረጸው ጣዖት፣ ሐሰትንም የሚናገር ምስል ምን ፋይዳ አለው? ሠሪው በገዛ እጁ ሥራ ይታመናልና፣ መናገር የማይችሉ ጣዖታትን ይሠራልና። ዕንጨቱን፣ ‘ንቃ!’ ሕይወት የሌለውንም ድንጋይ፣ ‘ተነሣ!’ ለሚል ወዮለት፤ በውኑ ማስተማር ይችላልን? እነሆ፤ በወርቅና በብር ተለብጦአል፤ እስትንፋስም የለውም። እግዚአብሔር ግን በተቀደሰ መቅደሱ አለ፣ ምድር ሁሉ በፊቱ ጸጥ ትበል።
ዕንባቆም 2:18-20 NASV

“ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ። “በላይ በሰማይ ወይም በታች በምድር ካለው ወይም በውሃ ውስጥ ከሚኖሩት ነገሮች በማናቸውም ምስል ለራስህ ጣዖትን አታብጅ። አትስገድላቸው፤ አታምልካቸውም፤ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ (ያህዌ ኤሎሂም) የሚጠሉኝን ልጆች ከአባቶቻቸው ኀጢአት የተነሣ እስከ ሦስትና አራት ትውልድ ድረስ የምቀጣ ቀናተኛ አምላክ (ኤሎሂም) ነኝ፤ ዘፀአት 20:3-5 NASV

“ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ። በላይ በሰማይ፣ በታች በምድር ላይ፣ ባለው ወይም ከምድር በታች ውሃ ውስጥ በሚኖር በማንኛውም ዐይነት ምስል ለራስህ ጣዖትን አታብጅ፤ እኔ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ)፣ የሚጠሉኝን ስለ አባቶቻቸው ኀጢአት እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድ ድረስ ልጆቻቸውን የምቀጣ ቀናተኛ አምላክ ነኝና። ለእነርሱ አትስገድላቸው፤ ወይም አታምልካቸው። ለሚወዱኝና ትእዛዛቴን ለሚጠብቁ ግን እስከ ሺህ ትውልድ ቸርነትንና ፍቅርን እገልጣለሁ። ዘዳግም 5:7-10 NASV

እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ጋር ኪዳን ሲገባ እንዲህ ሲል አዞአቸው ነበር፤ “ሌሎችን አማልክት አታምልኳቸው፤ አትስገዱላቸው፤ አታገልግሏቸው፤ አትሠውላቸውም፤ 2 ነገሥት 17:35 NASV

ስለዚህ ወዳጆቼ ሆይ፤ ከጣዖት አምልኮ ሽሹ። 1 ቆሮንቶስ 10:14 NASV

[7]

ሁለት ወይም ሦስት ሆነው በስሜ በሚሰበሰቡበት መካከል በዚያ እገኛለሁና።” ማቴዎስ 18:20 NASV

አካል ብዙ ብልቶች ቢኖሩትም አንድ አካል ነው፤ ነገር ግን ብልቶች ብዙ ቢሆኑም አካል አንድ ነው። ክርስቶስም እንደዚሁ ነው። አይሁድ ወይም የግሪክ ሰዎች ብንሆን፣ ባሪያ ወይም ነጻ ሰዎች ብንሆን፣ እኛ ሁላችን አንድ አካል እንድንሆን በአንድ መንፈስ ተጠምቀናልና፤ ሁላችንም አንዱን መንፈስ እንድንጠጣ ተሰጥቶናል። አካል የተሠራው ከብዙ ብልቶች እንጂ ከአንድ ብልት አይደለም። 1 ቆሮንቶስ 12:12-14 NASV

እያንዳንዳችን በአንዱ አካላችን ብዙ ብልቶች እንዳሉን፣ እነዚህም ብልቶች አንድ ዐይነት ተግባር እንደሌላቸው ሁሉ፣ እንዲሁም እኛ ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን። እያንዳንዳችንም የሌላው ብልት ነን። ሮሜ 12:4-5 NASV

አንድ ብልት ቢሠቃይ ብልቶች ሁሉ አብረው ይሠቃያሉ፤ አንድ ብልት ቢከብር ሌሎቹም ብልቶች አብረው ደስ ይላቸዋል። እንግዲህ እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ፤ እያንዳንዳችሁም የአካሉ ብልቶች ናችሁ። 1 ቆሮንቶስ 12:26-27 NASV

አንዳንዶች ማድረጉን እንደተዉት መሰብሰባችንን አንተው፤ ይልቁንም ቀኑ እየተቃረበ መምጣቱን ስታዩ እርስ በርሳችን እንበረታታ። ዕብራውያን 10:25 NASV

ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን፤ ክፉ የሆነውን ሁሉ ተጸየፉ፤ በጎ ከሆነው ነገር ጋር ተቈራኙ። እርስ በርሳችሁ በወንድማማች መዋደድ አጥብቃችሁ ተዋደዱ፤ አንዱ ሌላውን ከራሱ በማስበለጥ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ። ጌታን ለማገልገል በመንፈስ የጋላችሁ ሁኑ እንጂ ከዚህ ትጋት ወደ ኋላ አትበሉ። በተስፋ ደስተኞች ሁኑ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ። ችግረኛ ለሆኑ ቅዱሳን ካላችሁ አካፍሉ፤ እንግዶችን ተቀበሉ። የሚያሳድዷችሁን መርቁ፤ መርቁ እንጂ አትርገሙ። ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፤ ከሚያዝኑም ጋር እዘኑ። እርስ በርሳችሁ በመስማማት ኑሩ። ዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ካሉ ጋር አብራችሁ ለመሆን ፍቀዱ እንጂ አትኵራሩ፤ በራሳችሁም አትመኩ። ለማንም ክፉን በክፉ አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት በጎ የሆነውን ነገር ለማድረግ ትጉ። ቢቻላችሁስ በበኩላችሁ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ። ሮሜ 12:9-18 NASV

ወንድሞች ተስማምተው በአንድነት ሲኖሩ፣ እንዴት መልካም ነው! ምንኛስ ደስ ያሰኛል! መዝሙር 133:1 NASV

[8]

ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱ ወዳሉበት ቀርቦ እንዲህ አላቸው፤ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል፤ ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው፤ እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” ማቴዎስ 28:18-20 NASV

ያመነ የተጠመቀ ይድናል፤ ያላመነ ግን ይፈረድበታል። ማርቆስ 16:16 NASV

ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፤ “ንስሓ ግቡ፤ ኀጢአታችሁም እንዲሰረይላችሁ፣ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ። ሐዋርያት ሥራ 2:38 NASV

በመጓዝ ላይ ሳሉም ውሃ ካለበት ስፍራ ደረሱ፤ ጃንደረባውም፣ “እነሆ፤ ውሃ እዚህ አለ፤ ታዲያ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?” አለው። ፊልጶስም፣ “በፍጹም ልብህ ካመንህ መጠመቅ ትችላለህ” አለው። ጃንደረባውም፣ “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምናለሁ” ሲል መለሰለት፤ ሠረገላውም እንዲቆም አዘዘ። ከዚያም ሁለቱ አብረው ወደ ውሃው ወረዱ፤ ፊልጶስም ጃንደረባውን አጠመቀው። ሐዋርያት ሥራ 8:36-38 NASV

ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንድንሆን የተጠመቅን፣ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን? ስለዚህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሞት እንደ ተነሣ፣ እኛም እንዲሁ በአዲስ ሕይወት እንድንኖር በጥምቀት ሞተን ከእርሱ ጋር ተቀብረናል። ሮሜ 6:3-4 NASV

እነርሱም ይህን በሰሙ ጊዜ በጌታ በኢየሱስ ስም ተጠመቁ። ሐዋርያት ሥራ 19:5 NASV

ሁላችሁም በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁ፤ ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁላችሁ ክርስቶስን ለብሳችሁታልና። በአይሁድና በግሪክ፣ በባሪያና በነጻ ሰው፣ በወንድና በሴት መካከል ልዩነት የለም፤ ሁላችሁም በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ናችሁ። ገላትያ 3:26-28 NASV

በተጠራችሁ ጊዜ ወደ አንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ ሁሉ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ አንድ ጌታ፣ አንድ እምነትና አንድ ጥምቀት አለ፤ ከሁሉም በላይ የሆነ፣ በሁሉም የሚሠራ፣ በሁሉ የሚኖር የሁሉም አባት የሆነ አንድ አምላክ አለ። ኤፌሶን 4:4-6 NASV

በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፣ እርሱን ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር ኀይል በማመን ከእርሱ ጋር ደግሞ ተነሣችሁ። እናንተም በበደላችሁና የሥጋችሁን ኀጢአታዊ ባሕርይ ባለ መገረዝ ሙታን ሳላችሁ፣ እግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ሕያዋን አደረጋችሁ፤ ኀጢአታችንንም ሁሉ ይቅር አለን፤
ቈላስይስ 2:12-13 NASV

ይህም ውሃ አሁን የጥምቀት ምሳሌ ሆኖ ያድናችኋል፤ ይህም የሰውነትን እድፍ በማስወገድ ሳይሆን በንጹሕ ኅሊና በእግዚአብሔር ፊት የሚቀርብ መማፀኛ ነው፤ የሚያድናችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካይነት ነው፤ እርሱም ወደ ሰማይ ወጥቶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ፤ መላእክትና ሥልጣናት፣ ኀይላትም ተገዝተውለታል። 1 ጴጥሮስ 3:21-22 NASV

ታዲያ፣ አሁን ምን ትጠብቃለህ? ተነሥተህ ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ፤ ከኀጢአትህም ታጠብ።’ ሐዋርያት ሥራ 22:16 NASV

[9]

ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱ ወዳሉበት ቀርቦ እንዲህ አላቸው፤ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል፤ ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው፤ እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” ማቴዎስ 28:18-20 NASV

እንዲህም አላቸው፤“ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ፤ ያመነ የተጠመቀ ይድናል፤ ያላመነ ግን ይፈረድበታል። ማርቆስ 16:15-16 NASV

ቃሉን ስበክ፤ ጊዜው ቢመችም ባይመችም ዝግጁ ሁን፤ በታላቅ ትዕግሥትና በማስተማር አቅና፤ ገሥጽ፤ አበረታታም። ምክንያቱም ሰዎች ትክክለኛ የሆነውን ትምህርት የማይቀበሉበት ጊዜ ይመጣል፤ ከዚህ ይልቅ ለገዛ ምኞቶቻቸው የሚስማማውን፣ የሚያሳክክ ጆሮአቸው ሊሰማ የሚፈልገውን እንዲነግሯቸው በዙሪያቸው ብዙ አስተማሪዎችን ይሰበስባሉ። እውነትን ከመስማት ጆሮአቸውን ይመልሳሉ፤ ወደ ተረትም ዘወር ይላሉ። አንተ ግን በሁኔታዎች ሁሉ የረጋህ ሁን፤ መከራን ታገሥ፤ የወንጌል ሰባኪን ተግባር አከናውን፤ አገልግሎትህን ፈጽም። 2 ጢሞቴዎስ 4:2-5 NASV

[10]

ከክርስቶስ ጋር ከሞትን፣ ከእርሱ ጋር እንደምንኖር እናምናለን። ሮሜ 6:8 NASV

ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል። 1 ዮሐንስ 2:17 NASV

ምክንያቱም ጌታ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው እኛንም ደግሞ ከኢየሱስ ጋር አስነሥቶ ከእናንተ ጋር በፊቱ እንደሚያቀርበን እናውቃለን። ለብዙ ሰዎች እየደረሰ ያለው ጸጋ፣ ለእግዚአብሔር ክብር በምስጋና ላይ ምስጋናን እንዲጨምር ይህ ሁሉ ለእናንተ ጥቅም ሆኖአል። ስለዚህ ተስፋ አንቈርጥም፤ ውጫዊው ሰውነታችን እየጠፋ ቢሄድም እንኳ፣ ውስጣዊው ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል፤ ምክንያቱም ቀላልና ጊዜያዊ የሆነው መከራችን ወደር የማይገኝለት ዘላለማዊ ክብር ያስገኝልናል። ስለዚህ ዐይናችን የሚያተኵረው በሚታየው ነገር ላይ ሳይሆን በማይታየው ላይ ነው፤ የሚታየው ጊዜያዊ ነውና፤ የማይታየው ግን ዘላለማዊ ነው። 2 ቆሮንቶስ 4:14-18 NASV

[11]

እርሱም በሚሄድበት ጊዜ ትኵር ብለው ወደ ሰማይ ሲመለከቱ፣ እነሆ፤ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች ድንገት አጠገባቸው ቆሙ፤ እንዲህም አሏቸው፤ “እናንት የገሊላ ሰዎች ሆይ፤ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ እዚህ የቆማችሁት ለምንድን ነው? ይህ ከእናንተ ዘንድ ወደ ሰማይ ሲያርግ ያያችሁት ኢየሱስ፣ ልክ ወደ ሰማይ ሲወጣ እንዳያችሁት በዚሁ ሁኔታ ይመለሳል።” ሐዋርያት ሥራ 1:10-11 NASV

ደግሞም ከሙታን ያስነሣውንና ከሰማይ የሚመጣውን ልጁን፣ ከሚመጣውም ቍጣ የሚያድነንን ኢየሱስን እንዴት እንደምትጠባበቁ ይናገራሉ። 1 ተሰሎንቄ 1:10 NASV

በጌታ ቃል የምንላችሁ ይህን ነው፤ እኛ በሕይወት ያለንና ጌታ እስኪመጣ ድረስ የምንቀር ያንቀላፉትን አንቀድምም፤ ጌታ ራሱ በታላቅ ትእዛዝ፣ በመላእክት አለቃ ድምፅና በእግዚአብሔር የመለከት ድምፅ ከሰማይ ይወርዳልና። በክርስቶስ የሞቱትም አስቀድመው ይነሣሉ። ከዚያም በኋላ እኛ የቀረነው፣ በሕይወትም የምንኖረው ጌታን በአየር ላይ ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ በዚህም መሠረት ለዘላለም ከጌታ ጋር እንሆናለን። 1 ተሰሎንቄ 4:15-17 NASV

ስለዚህ ወዳጆች ሆይ፤ እነዚህን ሁሉ ነገሮች የምትጠባበቁ ስለ ሆናችሁ፣ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ከእርሱ ጋር በሰላም እንድትገኙ ትጉ። የጌታችን ትዕግሥት እናንተ እንድትድኑ እንደሆነ አስቡ፤ እንዲሁም ወንድማችን ጳውሎስ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፤ 2 ጴጥሮስ 3:14-15 NASV

“እነሆ፤ ቶሎ እመጣለሁ፤ ዋጋዬ በእኔ ዘንድ አለ፤ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍለዋለሁ። ራእይ 22:12 NASV

እነዚህን ነገሮች የሚመሰክረው፣ “አዎ፣ ቶሎ እመጣለሁ” ይላል። አሜን፤ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፤ ና። ራእይ 22:20 NASV